“ኢንቨስት ኢትዮጵያ” ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመት ፎረም በግንቦት ወር ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
“ኢንቨስት ኢትዮጵያ” ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመት ፎረም በግንቦት ወር ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 8/2017 (ኢዜአ ):-"ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2025" ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ግንቦት 4 እና 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይደረጋል።
የኢንቨስትመንት ፎረሙ በመንግስት ተቋማት፣የግሉ ዘርፍ እና የልማት አጋሮች የጋራ ትብብር የሚካሄድ ነው።
በፎረሙ ላይ ከዓለም ዙሪያ የተወጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ዓለም አቀፍ ሁነቱን ለማዘጋጀት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጀምሯል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፥ ፎረሙ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጭ ማስተዋወቅ እና የኢኮኖሚ እድገትን ማሳለጥ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።
የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተለወጠ በመጣው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስነ ምህዳር ዙሪያ እንደሚወያዩ አመልክተዋል።
የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ ተያይዞም የመንግስት እና የግል አጋርነት ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
በፎረሙ ላይ ባለሃብቶች፣የፋይናንስ ተቋማት፣የልማት አጋሮች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።