ተመራጮቹ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራጮቹ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር ተወያዩ
አሶሳ፤ መጋቢት 8/2017(ኢዜአ):- በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተመራጮች ከክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር ተወያዩ።
ውይይቱ የተደረገው የህዝብ ተወካዮቹ በክልሉ ከመራጮች ጋር ምክክር ሲያደርጉ ቆይተው የተነሱ ጥያቄዎችን መሠረት በማድረግ ነው።
በውይይቱ ላይ ሪፖርት ያቀረቡት የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል አቶ ሙባረክ ኤሊያስ፤ ከህብረተሰቡ ጋር በተደረገው ውይይት የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መነሳታቸውን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም የፌዴራል መንግስትን እገዛ የሚጠይቁ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት፣ የኔትወርክ ማሻሻያ፣ የመንገድ እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ተነስተዋል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ የጤና ተቋማት ግንባታ እና የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ተጠይቋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻደሊ ሐሰን በበኩላቸው፤ በህብረተሰቡ የተነሱት የልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ የመንገድ እና የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የተገኘውን ሰላም ለማፅናት ህብረተሰቡን ያሳተፈ የውይይት መድረክ እየተካሄደ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ -ጉባዔ አስካለች አልቦሮን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ አመራር አባላት ተገኝተዋል።