ቀጥታ፡

በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 53 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2017(ኢዜአ):- በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 53 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

መንግሥት ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ባደረገው ጥረት ከማይናማር እገታ ወጥተው ታይላንድ ወታደራዊ ካምፕ የነበሩ ዜጎችን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አመልክቷል።

በአካባቢው ከሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ትናንት 23፣ ዛሬ ደግሞ 30 በድምሩ በካምፑ የነበሩ 53 ዜጎች ተመልሰዋል።

እስከ አሁን በመጀመሪያውና ሁለተኛው ዙር ከማይናማር እገታ ወጥተው ታይላንድ ወታደራዊ ካምፕ የነበሩ 130 ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተደርጓል።

መንግሥት ሕብረተሰቡ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሀሰተኛ ቅስቀሳ ተታሎ የሥራ ስምሪት ውል ወዳልተፈፀመባቸው ሀገራት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብ ማሳሰቡን ሚኒስቴሩ በመረጃው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም