ቀጥታ፡

ባህላዊ የስፖርት ሀብቶችን በማልማትና በማስፋፋት ለሀገር ገፅታ ግንባታ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቷል 

ሆሳዕና፤ የካቲት 8/2017(ኢዜአ)፡-ባህላዊ የስፖርት ሀብቶችን በመጠበቅ፣ በማልማትና በማስፋፋት ለሀገር ገጽታ ግንባታ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህላዊ ስፖርቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።

"ባህላዊ ስፖርታችን ለጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ ሲካሄድ የቆየው 22ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና 18ኛው የባህል ስፖርት ፌስቲቫል ተጠናቋል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ህይወት መሀመድ እንዳሉት ኢትዮጵያ በርካታ ታሪክና የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች ያሏት ሀገር ናት።

ከእነዚህም ባህላዊ ስፖርቶች እንደሚጠቀሱ ገልጸው፤ የመደጋገፍና የመልካም ዕሴት ይዘት ያላቸውን ባህላዊ የስፖርት ሀብቶች በጥናት ታግዞ ለማልማት፣ ለማስፋፋትና ለማስተዋወቅ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ባህላዊ ስፖርትን ለማጠናከር ውድድሮችን ከማካሄድ ባለፈ የውድድር ሥነስርዓት ደንብ ለማዘጋጀትና ባህሉን ለማልማት የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

በኦሮሚያ ክልል የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ሀላፊ አቶ አብዲሳ ታዬ በበኩላቸው በየአካባቢው አብሮነትና ትስስርን የሚያጠናክሩ የባህል ስፖርቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

በዜጎች መካከል አብሮነት፣ ትስስርና ሰላምን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደ ባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫል ያሉ ኩነቶች ፋይዳቸው የጎላ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

ባህላዊ ፌስቲቫሉ ያሉንን ባህላዊ እሴቶች በስፋት ለማስተዋወቅ፣ ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግና ተሞኮሮን እርስ በርስ ለማስተዋወቅ ጠቀሜታ አንዳለውም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን አመራር አባል አቶ ባይነሳኝ ዘገየ በበኩላቸው፣ እንደሀገር እርስ በርስ የሚያስተሳስሩ በርካታ ባህላዊ ሀብቶችና እሴቶች እንዳሉ ጠቅሰው የባህላዊ ስፖርት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም