ተምሳሌቷ አርሶ አደር - ወይዘሮ ሃረጉ ጎበዛይ - ኢዜአ አማርኛ
ተምሳሌቷ አርሶ አደር - ወይዘሮ ሃረጉ ጎበዛይ

በተካ ጉግሳ መቀሌ (ኢዜአ)
አርሶ አደር ሃረጉ ጎበዛይ በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን የራማ ዓዲ አርባዕተ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። በአካባቢያቸው የግብርና ስራን የጀመሩት ከአካባቢ ጥበቃ ነው። ወትሮም ወደ ግብርና ስራ ያስገባቸው የሚኖሩበት አካባቢ ገላጣና አቧራማ ከመሆን ባለፈ ለኑሮ የማይመችና አረንጓዴ ልማትን በእጅጉ የሚሻ አካባቢ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነበር።
አርሶ አደሯ ከግብርና ስራ ውጪ ሌላ ስራ ያለም አይመስላቸው። ግብርናን ያልማሉ፤ ግብርናን ይኖራሉ፤ በግብርና ህይወታቸውን ለመቀየር ያቅዳሉ። ሆኖም ወደውት ሊገቡበት ያሰቡት የግብርና ስራ ከአካባቢው ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ግዙፍ ካፒታል እንደሚጠይቃቸው አስበዋል። አስበውም አልተቀመጡም በአንድ ወቅት አንዳች ነገር ለማድረግ ወሰኑ።
በቅድሚያ አርሶ አደሯ ሃረጉ አዕምሮ ላይ የተከሰተው ነገር እጄ ላይ ምን አለ የሚለው ነበር። በወቅቱ እጃቸው ላይ የነበረው ከሁለት ጥማድ መሬታቸው ያገኙት አንድ ኩንታል ዳጉሳ ነበር። ያንን አንድ ኩንታል ዳጉሳ ገበያ ወስደው በ1 ሺህ 500 ብር ይሸጡታል። ከዚያም ባገኙት ገንዘብ ምን ቢሰሩ እንደሚያዋጣቸው ለመወሰን በግላቸው የአዋጪነት ጥናት አደረጉ።
ከዚያም ካላቸው ሁለት ጥማድ መሬት ግማሽ ሄክታር የሚሆነውን መስኖን በመጠቀም የማንጎ ተክልን ቢያለሙ ምን ያህል ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ቀድመው አሰቡ። አርሶ አደሯ ወደ ማንጎ ልማቱ ከመግባታቸው በፊት ሊተገብሩት የሚገባ አንድ ብርቱ ጉዳይ እንዳለ አመኑ። እሱም አካባቢያቸውን በማልማት ወደ አረንጓዴነት መቀየር ቀዳሚው ነበር።
ከአካባቢያቸው አስተዳደር ጋር በመነጋገርም ያንን ድንጋያማ፣ የተቦረቦረና የግብርና ስራ ናፍቆት ጦም ያደረ መሬት ወደ አረንጓዴነት የመቀየር ተግባራቸውን ተያያዙት። በዚህም የተቦረቦሩ የመሬት ክፍሎችን በአፈር የመሙላትና የመደልደል ስራም የእርሳቸው ነበር።
እዚህ ጋር ከባዱ ስራ የነበረው አፈር ከሌላ ቦታ ማመላለሱ አድካሚ ሆኗል፤ ነገር ግን አርሶ አደሯ ግን ያስቀመጡት ራዕይ ከፊት ለፊታቸው እየታያቸው ነበርና የድካም ስሜቱ ሳያግዳቸው ተግባሩን በብቃት ፈፀሙት።
ባለቤታቸውን ከጎናቸው በማድረግም ቀድሞ በግማሽ ሄክታር ላይ ለማልማት አስበውት የነበረውን ልማት በጦም አደር መሬት ጋር ወደ 12 ሄክታር በማሳደግ ከማንጎ በተጨማሪ የአፕል ችግኞችን በመትከል ወደ ሰፊ ልማት ተሸጋገሩ። አርዓያነታቸው ተነሳሽነትን የፈጠረላቸው የአካባቢው አርሶ አደሮችም ከእርሳቸው ጋር ወደ ልማቱ በድፍረት እንዲገቡ አደረጓቸው።
አንድም ቀን ለሚያለሙት ልማት ዘመናዊ ማዳበሪያ ተጠቅመው እንደማያውቁ የሚናገሩት ወይዘሮ ሃረጓ የተፈጥሮ ማዳበሪያን የሁልጊዜ የግብረና ስራቸው አጋዥ ግብዓት በማድረግ እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ይናገራሉ። ይህንንም በወንዝ ውሃ ከሚወሰድ ደለል በማጠንፈፍ በማዘጋጀት እንደሚጠቀሙና ምርትና ምርታማነታቸውን እንዳሳደገላቸው ይገልጻሉ።
አርሶ አደሯ የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ሙያዊ ምክር በመቀበል እየተገበሩት የሚገኘው የግብርና ስራ በየጊዜው ውጤታማ እያደረጋቸው እንደሚገኝ አዘውትረው ይገልፃሉ። በቅርቡም ከአርባ ምንጭ በማምጣት የተከሉት ሙዝ ከአካባቢው አፈር ጋር መስማማቱን በግብርና ባለሙያዎች መረጋገጡን ገልፀዋል። ስለሆነም ዘሩን በማባዛት ጥቅም ላይ ለማዋል ዕቅድ እንዳላቸው አመልክተዋል።
አርሶ አደሯን ተምሳሌት ካደረጓቸው ተግባራት አንዱ ያለሙትን የማንጎም ሆነ የአፕል ችግኝ ለአካባቢው አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ለተግባር አጋሮቻቸው ህይወት መለወጥ የበኩላቸውን እየተወጡ መገኘታቸው ነው።
ለዚህም ይመስላል የሴት አርሶ አደር ወይዘሮ ሃረጉን ተሞክሮ ለማየት የግብርና ባለሙያዎች የምርምር አባላት የተካተቱበት ቡድን ሰሞኑን በአርሶ አደሯ ማሳ የተገኙት። በዚህም በራማ ዓዲ አርባዕተ ወረዳ የአርሶ አደሯን የተቀናጀ ልማት ምልከታ ተከናውኗል።
በወቅቱም የክልሉ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ገብረአምላክ በዛብህ(ዶ/ር) የአርሶ አደሯ ሥራ ግርምትን እንደፈጠረባቸው መስክረዋል። በወርሃ ግንቦትና ሰኔ አፕልና ማንጎ በየቀኑ ሁለት የጭነት ተሽከሪካሪዎችን ወደ ተለያዩ የክልሉ ከተሞች እና ወደ አዲስ አበባ ገበያዎች በመላክ በአማካይ በየቀኑ ከአንድ መኪና እስከ 650 ሺህ ብር ትርፍ የሚያገኙ መሆናቸውን ሲገልፁ ደግሞ የወይዘሮዋን ጥረትና ተምሳሌትነት በደንብ ያሳያል ብለዋል።
አርሶ አደሯ የገበያ ትስስራቸውን እስከ አዲስ አበባ በመዘርጋታቸው የገበያ ችግር እንደሌለባቸው ዘወትር ሲናገሩ እንደሚደመጡም መስክረዋል። የአካባቢው አርሶ አደሮች እየተደራጁ እንዲያለሙና በገበያ ትስስሩ በመጠቀም የገበያ ችግራቸውን እንዲቀርፉ እያደረጉ መሆኑንም አመልክተዋል። የአካባቢው አርሶ አደሮችም ዘወትር ይህንኑ ምስክርነት ይሰጧቸዋል።
ከነዚህም አንዱ አርሶ አደር ተክላይ ገብረ ይጠቀሳሉ። አርሶ አደሯ እያከናወኑት ያለው ጠንካራ ስራ ለእሳቸውም ተነሳሽነት ፈጥሮላቸው በመስኖ ልማት በመሳተፍ የእርሻ ማሳቸውን እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደሯ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ተነሳሽነትን ከማውረስ በተጨማሪ የአካባቢውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንድንችል ፈር ቀዳጅ እንደሆኑላቸውም አርሶ አደር ተክላይ መስክረዋል።
በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የመስኖና ሆልቲካልቸር ዳይሬክተር አቶ ሀይለ ታደለ በበኩላቸው፡ የአርሶ አደሯ እንቅስቃሴ መንግስት ቀጣይነት ያለው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን ለማስፋት እያደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
አካባቢውን የፍራፍሬ ልማት ማእከል/ስፔሻላይዝ/ የማድረግ ዓላማ እንዳላቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ሃረጉ ጎበዛይ፣ አሁን ላይ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ 50 ሺህ የማንጎ እና የአፕል ችግኞችን እያፈሉ ለአካባቢው አርሶ አደሮች በተመጣጠኝ ዋጋ ለማከፋፈል እንደተዘጋጁም ገልፀዋል።