ኮሚሽኑ በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አጀንዳዎችን የማደራጀትና የመቅረጽ ስራ ያከናውናል - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አጀንዳዎችን የማደራጀትና የመቅረጽ ስራ ያከናውናል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በምክክሩ ሂደት እስካሁን የተሰባሰቡና በቀጣይ የሚሰባሰቡ አጀንዳዎችን የማደራጀትና የመቅረጽ ስራዎች እንደሚያከናውን ገለፀ፡፡
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ባለፉት ሶስት ዓመታት አካታችና አሳታፊ የሆነውን ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።
ሀገራዊ ምክክሩን የማካሄድ፣ ከምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሀሳቦችን ማጠናቀር እና ተፈፃሚነታቸውን የመከታተል ስራዎች እንደሚተገበሩም ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ እስካሁን ባስመዘገባቸው ውጤቶች የሁሉም አካላት ተሣትፎ የላቀ እንደነበር በመጠቆም፣ ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የአጀንዳ ማሰብሳብ ሂደቱም በአብዛኛው ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በስኬት መጠናቀቁን አንስተዋል።
ኮሚሽኑ በቀሪ ጊዜያት የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ባልተከናወነባቸው አካባቢዎች የማጠቃለል ሥራን እንደሚያከናውን ጠቅሰዋል።
በአማራ ክልልም የተሳታፊዎች ልየታ በመከናወኑ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንደሚገባ አንስተው፤ለዚህም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።