ቀጥታ፡

በፍርድ ቤቱ የተመቻቸው አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርአት ከእንግልትና ውጣ ውረድ ታድጎናል--ተገልጋዮች

ጎንደር፤ መጋቢት 6/2017(ኢዜአ)--የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያመቻቸው አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓት ይደርስባቸው ከነበረ እንግልትና ውጣ ውረድ እንዳታደጋቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡

የሙግት መፍቻ ሥርዓቱ ሁለት ተከራካሪ ወገኖች በመረጧቸው አስታራቂ ሽማግሌዎች አማካኝነት በፍርድ ቤት አስማሚነት ጉዳያቸውን በእርቅና በስምምነት ታይቶ የሚያልቅ በመሆኑ የፍርድ ቤቶችን ጫና ማቃለሉም ተመላክቷል። 

የጎንደር ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ብርቱካን ማሞ በሰጡት አስተያየት፤  የልጅ ቀለብ ይቆረጥልኝ በሚል የጀመሩት የህግ ክርክር በአማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓት እልባት በማግኘቱ ፋይሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ መዘጋቱን ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ያመቻቸው አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓት ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸውን በእርቅና በስምምነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያጠናቅቁ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑንም ነው የተናገሩት። 

በገንዘብ መካካድ ሳቢያ በፍርድ ቤት የመሰረቱት ክስ በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ አማራጩ የሙግት መፍቻ ስርዓት እንዳገዛቸው የተናገሩት ሌላው የከተማው ነዋሪ ደግሞ አቶ ሰለሞን አበራ ናቸው።

የመሰረቱት ክስ ፍርድ ቤቱ ባመቻቸው የእርቅና የስምምነት ሂደት መፈታቱ ለጠበቃና ለማመልከቻ ማጻፊያ ያወጡት የነበረውን ወጪና እንግልት ማስቀረቱንም ተናግረዋል፡፡

ሌላው የጎንደር ከተማ ነዋሪ አቶ ዘመድኩን በላይ ፤ "የሙግት መፍቻ ሥርዓቱ ባህላዊ ሽምግልናችንን የተከተለ በመሆኑ እኔም የሥርአቱ ተጠቃሚ ሆኛለሁ" ብለዋል፡፡

ከእርሻ መሬት ይዞታ መጋፋት ጋር በተያያዘ የመሰረቱት ክስ በእርቅ እንዲያልቅ ፍርድ ቤቱ በሰጣቸው ምክረ ሃሳብ መሰረት በመረጡት ሽማግሌ አማካኝነት ክርክሩ እልባት አግኝቶ የክስ መዝገቡ መዘጋቱን ገልጸዋል፡፡ 

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ቸርነት ተገኘ በበኩለቸው፤ በአማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓቱ የህዝብና የመንግስት ጥቅሞችን የሚጎዱ ከፍተኛ ወንጀሎች አይካተቱም።

የሙግት መፍቻ ሥርዓቱ ሁለት ተከራካሪ ወገኖች በመረጧቸው አስታራቂ ሽማግሌዎች አማካኝነት በፍርድ ቤት አስማሚነት ጉዳያቸው በእርቅና በስምምነት የሚያልቅበት ሥርአት በመሆኑ የፍርድ ቤቶችን ጫና እያቃለለ መሆኑን ተናግረዋል።

ሥርዓቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ጨምሮ በጎንደር ከተማና ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ባሉ መደበኛ ፍርድ ቤቶችም በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የህዝብ ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በአማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓት እንዲፈቱ ከመራቸው የህግ ክርክሮች 179ኙ እልባት በማግኘታቸው የከስ መዝገቦቹ እንዲዘጉ ፍርድ ቤቱ ማጽደቁንም አቶ ቸርነት ገልፀዋል፡፡ 

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፉት ስድስት ወራት ከተመለከታቸው የክስ መዝገቦች መካከል ከ14 ሺህ በላይ ለሚሆኑት እልባት መስጠቱም ታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም