ቀጥታ፡

"ስሜ ደበላ ታላቁ የግብርና ምርምር ሥርዓት መሪ"በሚል ርዕስ የተጻፈ መፅሐፍ ተመረቀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 06/2017(ኢዜአ)፦ የዶክተር ስሜ ደበላን የህይወት ታሪክ የሚዳስስ "ስሜ ደበላ ታላቁ የግብርና ምርምር ሥርዓት መሪ" የተሰኘው መፅሐፍ ተመረቀ፡፡

”ስሜ ደበላ ታላቁ የግብርና ምርምር ስርዓት መሪ”  የተሰኘውን እና በደራሲ ገስጥ ተጫኔ ተፅፎ የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ ያሳተመውን የህይወት ታሪክ መፅሀፍ የሙያ አጋሮቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው  በተገኙበት በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመርቋል፡፡

በመፅሃፉ ቀዳሚ ቃል እንደሰፈረው፤ ዶክተር ስሜ በኢትዮጵያ ጠንካራ አገራዊ የግብርና ምርምር ሥርዓት እንዲሰፍን መሠረት ከጣሉት መካከል አንደኛው ናቸው።

ዶክተር ስሜ ሙያቸውን የጀመሩት በከፍተኛ የገብስ ተመራማሪነት ሲሆን፤ በወቅቱ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በሆለታ ምርምር ማዕከል፣ በአሁኑ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እንደነበር በቀዳሚ ቃል ላይ ተገልጿል።

በ1980ዎቹ መጀመሪያ የግብርና ምርምር ተቋም አምስተኛው ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዶክተር ስሜ የግብርና ምርምር ሥርዓቱን ለመለወጥ የነበራቸውን ህልም እውን ለማድረግ ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ እንዳስቻላቸው ተጠቁሟል።

ዶክተር ስሜ አግሮኮሎጂን መሰረት ያደረጉ የምርምር ማዕከላት ተቋቁመው ምርትን መሰረት ያደረጉ የምርምር ሥራዎች በተመረጡ የምርምር ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ያረጋግጡ እንደነበርም ነው የተጠቆመው።  

መፅሐፉ የዶክተር ስሜ ደበላን የህይወት ታሪክን  አስደናቂ ልምድና ተሞክሯቸውን የሚዳስስ መሆኑ በመድረኩ ተመላክቷል፡፡

ዶክተር ስሜ ደበላ በበርካታ ቦታዎች  የስራ ሃላፊነት ያገለገሉ ጠንካራ አመራር እንደነበሩ ተገልጿል፡፡

የመጽሃፉ ጸሀፊ ደራሲ ገስጥ ተጫኔ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የዶክተር ስሜ ደበላን ታሪክ ለመጪው ትውልድ ትምህረት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሣ  በበኩላቸው፤ ዶክተር ስሜ ደበላ  በኢትዮጵያ ግብርና መስክ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ለትውልዱም ታሪክ እንዲሆን የዚህን ታላቅ ምሁር መፅሐፍ  በኢትዮጵያሣይንስ አካዳሚ ፕሬስ እንዲታተም መደረጉን ተናግረዋል፡፡ 

የዶክተር ስሜ ደበላ ባለቤት ወይዘሮ አለምጸሃይ ወልደሰማያት እንደገለጹት፤በህይወት ዘመኑ በነበረበት ወቅት ታሪኩ በመጽሃፍ እንዲሰነድ እና ለትውልድ ታሪክ ሆኖ እንዲቀመጥ ብዙ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የባለቤታቸው ህይወት ካለፈ በኋላ ታሪካቸው እንዲሁ እንዲቀር ባለመፈለጋቸው ታሪኩ ተሰንዶ መጽሃፉ መታተም መቻሉን ገልጸው፤ ትብብብር ላደረጉ አካላትም ምስጋናቸውን አቅረበዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም