ብልፅግና ፓርቲ ለ5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና ለ2ኛ ጉባኤው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና መርሐ ግብር እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ ለ5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና ለ2ኛ ጉባኤው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና መርሐ ግብር እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፤መጋቢት 6/2017(ኢዜአ)፦ብልፅግና ፓርቲ ለ5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና ለ2ኛ ጉባኤው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሃብቶችና የተቋማት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እንዲሁም በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መከበሩ ይታወሳል።
የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ደግሞ "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከጥር 23 እስከ 25/2017 ዓ.ም ተካሂዷል።
ከ15 ሀገራት የተውጣጡ የጎረቤት ሀገራት እና የብሪክስ አባል ሀገራት እህት ፓርቲዎች አመራሮች ጭምር የተሳተፉበት የፓርቲው 2ኛ ጉባኤ በርካታ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች የተላለፉበት ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ለብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና ለፓርቲው 2ኛ ጉባኤ ስኬት ላበረከተው አስተዋጽኦ ዕውቅና ተሰጥቶታል።
ፓርቲው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያበረከተውን የምስጋና እና የዕውቅና የምስክር ወረቀት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ከፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እጅ ተረክበዋል።
ሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የግል ተቋማትን ጨምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላት ምስጋና እና እውቅና ተሰጥቷቸዋል።