ሉሲዎቹ ወደ ቀጣዩ ዙር አላለፉም - ኢዜአ አማርኛ
ሉሲዎቹ ወደ ቀጣዩ ዙር አላለፉም
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በካሜሮን አቻው በደርሶ መልስ ውጤት ተሸንፏል።
ብሄራዊ ቡድኑ ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ስታዲየም ባደረገው የመልስ ጨዋታ በካሜሮን 1 ለ 0 ተሸንፏል።
ታዛኑ አንጌ በ13ኛው ደቂቃ ለካሜሮን የማሸነፊያዋን ጎል አስቆጥራለች።
ውጤቱን ተከትሎ ካሜሮን በድምር ውጤት 6 ለ 2 በማሸነፍ የመጨረሻውን ዙር ተቀላቅላለች።
ሀገራቱ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ያውንዴ ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ካሜሮን 5 ለ 2 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
ካሜሮን በመጨረሻው ዙር ከዩጋንዳ እና ኬንያ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።
ዘጠነኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በሞሮኮ አዘጋጅነት በጥቅምት እና ህዳር ወር 2018 ዓ.ም ይደረጋል።
በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። ከሞሮኮ ውጪ አፍሪካ አራት ሀገራትን የማሳተፍ ኮታ አላት።