የሲዳማ ቡናን የጥራት መለያ መፅሐፍ ለማዘጋጀት የሚያስችል የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የሲዳማ ቡናን የጥራት መለያ መፅሐፍ ለማዘጋጀት የሚያስችል የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2017(ኢዜአ)፦የሲዳማ ቡና መልክዓ ምድራዊ አመላካች የሚያሳይ የጥራት መለያ መፅሐፍ ለማዘጋጀት የሚያስችል የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር ናቸው የተፈራረሙት።
የጥራት መለያ መፅሐፉ የምርቱን ስም፣ መገኛ ቦታ፣ የሚመረትበትን መንገድ፣ በምርቱና በመገኛ ቦታው መካከል ያሉ ግንኙነቶችንና የመሳሰሉትን የሚያካትት ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል በዚሁ ወቅት፤ ባለስልጣኑ በአዕምሯዊ ንብረት፣ በንግድ ምልክትና የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ላይ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
መልክዓምድራዊ አመላካች የመብት ጥበቃ እንዲያገኝ ህግ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፤ በዛሬው ስምምነት መሰረትም ለሲዳማ ቡና የጥራት መለያ መጽሐፍ ይዘጋጃል ብለዋል።
የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ታፈሰ ማቲዮስ (ዶ/ር) በሲዳማ ቡና ላይ የሚጀመረውን የጥራት መለያ መፅሐፍ ዝግጅት ለማሳካት በምርምርና የማማከር ስራዎች እናግዛለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ዘሪሁን ቃሚሶ ተፈራ በበኩላቸው፤ መልክዓ ምድራዊ አመላካቹ መፅሐፍ የአርሶ አደሩንና የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያስችላል ነው ያሉት።
የመልክዓ ምድራዊ አመላካች አንድ ተለይቶ በታወቀ አካባቢ የተመረተ ምርት በሸማቾች ዘንድ የሚታወቅበት ጥራትና ዝና ያለው ከሆነና ጥራትና ዝናው ከተመረተበት አካባቢ ጋር የተቆራኘ ሲሆን ከሌሎች ምርቶች ለመለየት የሚያገለግል ምልክት ነው።