ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብር እና ሀገር አቀፍ የቁርአን ውድድር ፍጻሜ ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብር እና ሀገር አቀፍ የቁርአን ውድድር ፍጻሜ ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 06/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብር እና ሀገር አቀፍ የቁርአን ውድድር ፍጻሜ ነገ በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ በሰጡት መግለጫ በሀገር አቀፍ ደረጃ የቁርአን ውድድር ማጣሪያ "ቁርአን የእውቀትና የሰላም ምንጭ" በሚል መሪ ሐሳብ ሲካሄድ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
በዙር በተካሄዱ ውድድሮችም ነገ ለሚካሄደው የፍጻሜ ውድድር ከሁለቱም ጾታዎች ሦስት ሦስት ተወዳዳሪዎች መለየታቸውን ተናግረዋል።
ውድድሩ ወጣቶች ሃይማኖታዊ አስተምህሮን የበለጠ እንዲገነዘቡ ከማድረግ ባለፈ ጥሩ ስነምግባር ያለው ዜጋ በመፍጠር በኩል አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
በሌላ በኩል ሀገር አቀፍ ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብር እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በዚህ አብሮነትንና አንድነትን በሚያጎላው ታላቅ ሥነ ስርዓት ላይ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንደሚታደሙም ገልፀዋል።