የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት መጠናቀቅ የሀገር ፍቅር ስሜትንና የሙያ ብቃትን የሚያስመሰክር ነው - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት መጠናቀቅ የሀገር ፍቅር ስሜትንና የሙያ ብቃትን የሚያስመሰክር ነው - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት መጠናቀቅ የሀገር ፍቅር ስሜትን እና የሙያ ብቃትን የሚያስመሰክር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና 46ኛው የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች የምስጋናና የዕውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩም የኢትዮጵያ ዜና አግልግሎት (ኢዜአ)ን ጨምሮ የመገናኛ ብዙኃን፣ የፀጥታና ደኅንነት፣ የሆቴልና ቱሪዝም፣ የንግድና የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ግለሰቦች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፤ ጉባኤው የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነትና የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት ያስተዋወቀ ነው ብለዋል።
የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልና የኮሪደር ልማትም መዲናዋ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በምቹና አስተማማኝ መሰረተ ልማት የማስተናገድ አቅም እንዳላት አስመስክረዋል ብለዋል።
የሕብረቱ ጉባኤ ተሳታፊ ሀገራት መሪዎችም በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በከተሞቻቸው ለመተግበር ትምህርትና መነሳሳት የወሰዱበት አኩሪ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያም እንደ አስተናጋጅና አባል ሀገር አህጉሪቷን የሚበጁ የሰላምና ደህንነት፣ የልማትና የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረጓን አስረድተዋል።
የሕብረቱ ስኬታማ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባልነት ምርጫም ቀጣናዊና አህጉራዊ አጀንዳዎችን ለመቅረጽና አቋሞችን ለማራመድ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኅንም የመሪዎችን መልዕክት በማስተላለፍ ፓን አፍሪካኒዝምን የሚያወሱና በሚያቀጣጥሉ አዎንታዊ መረጃዎችን በማሰራጨት ገንቢ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰዋል።
በሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የቀረቡ አጀንዳዎችና የሱዳን ሰብዓዊ ድጋፍ የጎንዮሽ መድረክም ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ስኬትም በሀገር ፍቅር ስሜትና በሙያ ብቃት በትብብር የመከናወኑ የስራ ውጤት መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም ለ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 46ኛው የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የጉባኤው ዝግጅት የብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ ጉባኤው የኢትዮጵያን በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ተጠቃሚነት በማሳደግ በስኬት ተጠናቋል ብለዋል።
የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤና የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ የኢትዮጵያዊያንን የዕንግዳ ተቀባይነት ባህል በሚያንጸባርቅ መልኩ በስኬት ተካሂዷል ብለዋል።
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና 46ኛው የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ "የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ ከየካቲት 05 እስከ 09/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።