ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ከፍታና የዓለም አቀፍ አብሮነት መገለጫችን ነው - ዑስታዝ አቡበከር አሕመድ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 06/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ከፍታና የዓለም አቀፍ አብሮነት መገለጫ መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዑስታዝ አቡበከር አሕመድ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የረመዳን ፆምን ምክንያት በማድረግ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ትናንት ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል የኢፍጣር መርሐ ግብር አካሂዷል።


 

በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ለማ ያደቻ፤ በየዓመቱ የሚዘጋጀው የኢፍጣር መርሃ ግብር አብሮነትን ለማሳየት ያለመ ነው ብለዋል።


 

ብሔራዊ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት በማገልገል የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በኢፍጣር መርሃ ግብሩ ለተሳተፉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዑስታዝ አቡበከር አሕመድ፤ የረመዳን ወርን ምክንያት በማድረግ የኢፍጣር መርሃ ግብር በመዘጋጀቱ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀጂ ጉዞ ሥራ ላይ የመስተንግዶና አስፈላጊ የውጭ ምንዛሬ እገዛ በማድረግ ጭምር ከዓመት ዓመት የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በዚህም የአየር መንገድ የኢትዮጵያ ከፍታና የዓለም አቀፍ አብሮነት መገለጫ ሆኗል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያኮራና የሚያስደስት ስራ እያከናወነ ነው ያሉት ዑስታዝ አቡበከር፤ በቀጣይም በተሻለ ከፍታ በአብሮነትና በመቀራረብ የምንጓዝ ይሆናል ብለዋል።

ረመዳን የአብሮነትና የከፍታ ወር በመሆኑ ሀገራዊ አብሮነት፣ መረዳዳት፣ መተሳሰብና መከባበርን በማጠናከር አዲስ ምዕራፍ የሚከፈትበት ወር መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህን በማጠናከር በአብሮነትና እኩልነት የኢትዮጵያን ከፍታ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት።

በመርሐግብሩ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሸኽ አብዱልአዚዝ አብዱል ወሊ፣ የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሡልጣን አማን ኤባ፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም