የኢትዮጵያ የስልጠና ተቋማት የዓለም አቀፉ የትምህርት ተቋማት ሥራ አመራር ስርዓት እውቅና አገኙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የስልጠና ተቋማት የዓለም አቀፉ የትምህርት ተቋማት ሥራ አመራር ስርዓት እውቅና አገኙ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2017(ኢዜአ)፦ ሰባት የኢትዮጵያ ስልጠና ተቋማት የዓለም አቀፉ የትምህርት ተቋማት ሥራ አመራር ስርዓት በማሟላት እውቅና ማግኘታቸውን የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት (ISO 21001: 2018) እና የባለሙያ ዕውቅና (ISO 17024:2012) ሥራ አመራር ስርአትን በመተግበር ሂደት የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱን ከኢንስቲትዩቱ ጋር የተፈራረሙት 46 የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት እና የሁሉም ክልሎችና የሁለቱም ከተማ አስተዳድሮች የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ኤጀንሲንዎች ናቸው።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሚኒስቴሩ የሥራ ገበያው የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው።
በዚህም ተቋማት የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን እንዲተገብሩ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።
በእስከ አሁኑ ሂደትም የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩትን ጨምሮ ሰባት የስልጠና ተቋማት የዓለም አቀፉ የትምህርት ተቋማት ሥራ አመራር ስርአትን በማሟላት እውቅና እንደተሰጣቸውም አመልክተዋል፡፡
ተወዳዳሪና ብቁ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የማሰልጠኛ ተቋማት ብቻ ሳይሆን የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የሚሰጡት ተቋማትም ጭምር የጥራት ሥራ አመራር ስርአቱን መተግበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ስምምነቱ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ 14ቱም የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከላት የISO 17024:2012 ደረጃ እንዲያሟሉ የሚያስችል እንደሆነም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።
የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድምአገኝ አሰፋ በበኩላቸው፤ መንግሥት ለጥራት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን መፍጠር የሚያስችል ግዙፍ የጥራት መንደር ተገንብቶ ወደ ስራ ገብቷል ብለዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ደረጃዎችን በመተግበር ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንደሚገባቸው ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።