የኢትዮ-ቻይና አጋርነት የቻይና-አፍሪካ ትብብር ምሳሌ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ቻይና አጋርነት የቻይና-አፍሪካ ትብብር ምሳሌ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2017(ኢዜአ)፦ በመተማመንና መከባበር ላይ የተመሰረተው የኢትዮ-ቻይና የሁለትዮሽ አጋርነት የቻይና-አፍሪካ ትብብር ሁነኛ ምሳሌ መሆኑን በቻይና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና አስተባባሪ ሲድሃርት ቻተርጂ ገለፁ።
በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩበትን 55ኛ ዓመት በቤጂንግ አክብሯል።
በስነ ስርዓቱ ላይ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው፣ የቻይና መንግስት አመራሮች፣ ተቀማጭነታቸውን በቻይና ያደረጉ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
አምባሳደር ተፈራ ደርበው በዓሉን አስመልክቶ ከሲጂቲኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ለረጅም ጊዜ የዘለቀው የኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ትብብር በጋራ መተማመን እና መከባበር እንዲሁም እኩልነት የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት ላለፉት 55 ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ እና ለረጅም ጊዜ ጸንቆ የቆየ አጋርነት መፍጠራቸውን አመልክተዋል።
በጠንካራ መሰረት ላይ የሚገኘውን የሀገራቱን ግንኙነት ለቀጣይ ትብብራቸው እና አጋርነታቸው መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
በሁነቱ ላይ የተገኙት በቻይና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና አስተባባሪ ሲድሃርት ቻተርጂ ኢትዮጵያ የቻይና-አፍሪካ ትብብር ትክክለኛ ምሳሌ ሆና የምትጠቀስ ሀገር ናት ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚው መስክ ያላቸው ትስስር በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ተመድ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በመልካም ጎኑ እንደሚያየው ገልጸው ፍላጎታችን አፍሪካ እንድታድግ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በቻይና የአፍሪካ ዲፕሎማቶች ጓድ ዲን የሆኑት በቻይና የካሜሮን አምባሳደር ማርቲን ምፓና ኢትዮጵያ እና ቻይና ፍሬያማ የሁለትዮሽ ግንኙነት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለቻይና-አፍሪካ ትብብር በምሳሌነት የሚጠቀስ እንደሆነ መናገራቸውን የሲጂቲኤን ዘገባ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1970 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።