ኢትዮጵያውያን በኡጋንዳ በተለያየ የንግድ ዘርፍ በመሰማራት ውጤታማ እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በኡጋንዳ በተለያየ የንግድ ዘርፍ በመሰማራት ውጤታማ እየሆኑ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያዊያን በኡጋንዳ በፋሽን፣ ልብስና ሆቴል ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች በመሰማራት ውጤታማ ተግባራት እያከናወኑ እንደሚገኙ ተገለጸ።
በኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር ጆን ሙሂንዲ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡
በኡጋንዳ በርካታ ኢትየጵያዊያን በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ የንግድ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በተለይም በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ኢትየጵያውያን በተለያየ የንግድ ዘርፍ በመሰማራት በርካታ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በዋና ከተማዋ ኢትየጵያዊያን በፋሽን፣ በልብስና በሆቴል ዘርፍ እንዲሁም የንግድ ዘርፎች በመሰማራት ውጤታማ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
ይህ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች የንግድ ስራ በካምፓላ ብቻ ሳይወሰን በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
በንግዱ ዘርፍ የኢትዮጵያ ዜጎች እያከናነወኑት ያለው ውጤታማ ስራ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት በማጠናከር በኩል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በካምፓላ በርካታ ነጋዴዎች ያሉ ሲሆን የተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተዋል ያሉት ኃላፊው ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ የንግድ አካባቢ ተብሎ የሚጠራ ቦታ መኖሩንና በዚህ ንግድ ቦታ የምታጣው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
ልብስ መሸጫዎች፣ ሆቴሎች ታገኛለህ የኢትዮጵያን ምግብ እንጀራ መብላት ብትፈልግ ማግኘት ትችላለህ ሲሉ ይገልጻሉ።
የኡጋንዳ የመንግስት ልዑካን ቡድን በቅርቡ በኢትዮጵያ በመገኘት የኢትየጵያ ዲያስፖራ በልማት እያደረገ ያለው ተሳትፎ ላይ የልምድ ልውውጥ ማድረጉ ይታወሳል።