ኢትዮጵያ በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥታለች- አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥታለች- አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ባከናወነቻቸው ስራዎች ትልቅ ለውጥ ማስመዝገቧን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ ገለጹ።
69ኛው ዓለም አቀፉ የሴቶች ጉዳይ ኮሚሽን መደበኛ ስብስባ በተመድ ዋና መቀመጫ ኒው ዮርክ መካሄድ ከጀመረ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ በስብስባው ላይ በሴቶች ጉዳይ ላይ እያከናወነች ያለውን ስራ አስመልክቶ ንግግር አድርገዋል።
አምባሳደር ሳሙኤል ኢትዮጵያ በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ባደረገው የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሃ ግብር የተቀመጡ የትኩረት መስኮችን መሰረት በማድረግ ባከናወችው ስራ በርካታ ለውጦችን ማምጣቷን ገልጸዋል።
ለዚህ ብሔራዊ የትኩረት አቅጣጫዎች እና የመንግስት ቁርጠኝነት የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን አመልክተዋል።
በሁሉም ደረጃ ያለው ፍትሃዊ የሴቶች ውክልና ለስኬቱ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
69ኛው ዓለም አቀፉ የሴቶች ጉዳይ ኮሚሽን መደበኛ ስብስባ እስከ መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ ኢዜአ በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የሴቶች ጉዳይ ኮሚሽን በስርዓተ ጾታ እኩልነት፣ የሴቶች መብቶች መከበር እና ማብቃት ላይ የሚሰራ ዓለም አቀፍ የበይነ መንግስታት ተቋም ነው።