ኢትዮጵያና ሩዋንዳ በአካባቢያዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ መከሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ሩዋንዳ በአካባቢያዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ መከሩ
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፦ የሩዋንዳ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሙባረክ ሙጋጋ እና የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በአካባቢያዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ እንዳመለከተው የሩዋንዳው ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሙባረክ ሙጋጋ ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ ጋር ባደረጉት ውይይት በሁለቱ ሀገራት እና በአካባቢው ፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም በሀገራቱ ወታደራዊና የደኅንነት አቅም ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ምክክር አድርገዋል።
የሩዋንዳ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም በአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የተከናወኑት የሪፎርም ትግበራ ሂደት የሚያሳየውን የተቋሙን ኢንተለጀንስ ፊውሽን ሴንተር(Intelligence fusion center) እና የዲጂታል ኤግዚቢሽንን ጎብኝተዋል።
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና ተቋማዊ አሰራር የሪፎርም ሥራዎችን ተከትሎ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ተቋሙ የሀገሪቱን ብሄራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚያስችል ከፍ ያለ አቅምና ደረጃ ላይ እንዲገኝ ማስቻሉን በሠጡት አስተያያት ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሩዋንዳ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሙባረክ ሙጋጋ ባለፈው ሳምንት የተመረቀውንና የሲቪል፣ ወታደራዊና የደኅንነት አገልግሎት የሚሠጡ ድሮኖችን ለማምረት የተቋቋመውን የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ የድሮን ማምረቻ ፋብሪካ ተዘዋውረው በመጎብኘት፤ ኢትዮጵያ በወታደራዊና ደኅንነት ዘርፍ በደረሰችበት ልህቀት መደነቃቸውን አያይዘው ገልጸዋል።