ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን የህብረተሰብ ጤና ስርዓት እየገነባች ነው - የዓለም ጤና ድርጅት

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ጠንካራ የህብረተሰብ ጤና ስርዓት እየገነባች መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ረዳት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቺክዌ ኢሂክዋዙ ገለፁ።

ዶክተር ቺክዌ ኢሂክዋዙ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስራ እንቅስቃሴን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነች ያለው ተግባር ጠንካራ የጤና ስርዓት ለመዘርጋት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም ዳይሬክተሩ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡


 

በጤናው ዘርፍ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን መረዳታቸውን ጠቅሰው በዘርፉ የመሠረተ ልማት እና የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ አቅምን በማሻሻል በኩል የታዩ እድገቶችን አድንቀዋል።

እነዚህም ኢትዮጵያ ጠንካራ እና የማይበገር የጤና ስርዓት ለመዘርጋት ያላትን ቁርጠኝነት በግልፅ የሚያመላክቱ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በመላው ዓለም በማሕበረሰብ ጤና መስክ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት እንዲጠናከሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።


 

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚሆን ነው ያስታወቁት።

የዓለም ጤና ድርጅት ለኢንስቲትዩቱ ስራዎች ውጤታማነት ድጋፉን እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።

ተቋሙ እየሰራቸው ያሉ የምርምርና የልማት ስራዎች የአህጉሪቱን የጤና ስርዓት በእጅጉ የሚያሻሻሉ መሆናቸውን መገንዘባቸውን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ምሳሌ የሚሆን ሥራን እያከናወነች ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የጤና ዘርፉን የተሻለ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ስራዎቹ በራስ አቅም፣ በህብረተሰብ ተሳትፎ እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የህብረተሰብ አደጋ ቁጥጥርና የበሽታ ቅኝት ምላሽ የሚሰጥባቸው ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል።

የህብረተሰብ ጤና ምርምር፣ የላቦራቶሪ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስራዎች ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ ከምትሰራቸው መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም