የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስከብሩ የዘገባ ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስከብሩ የዘገባ ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፡- የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስከብሩ ዘገባዎችን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተጠቆመ።
ለዚህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚናዋን እና ተለዋዋጭ የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታን በቅጡ መገንዘብ እንደሚገባ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትና ከሆርን ሪቪው ጋር በመተባበር በዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታ እና ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዮት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በረከት ድሪባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ጥቅም በማስከበር ረገድ የላቀ ሚና ይጫወታሉ።
ለዚህም የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ፍላጎት መረዳት እንደሚገባ ጠቁመው፤ መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ፋይዳ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትም የመገናኛ ብዙሃንን አቅም የሚያጎለብቱ ሥራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ(ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አካሄድና ዓለም አቀፋዊ ለውጦችን መገንዘብ የኢትዮጵያን ጥቅም በተሻለ መልኩ ለማስከበር አጋዥ መሆኑን አንስተዋል።
የመደመር እሳቤን ከኢትዮጵያ አልፎ አህጉራዊ አጀንዳ ማድረግና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ከመንግሥት ተኮር ወደ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መሸጋገሩን ታሳቢ ያደረገ የዘገባ ሥራ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉም የልማት መስክ ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኗን መገናኛ ብዙኃን አጽንኦት ሊሰጡት ይገባል ነው ያሉት።
ዘላቂ የሰላም ግንባታና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ትኩረት የሚሹ መሆናቸውንም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያብራሩት፡፡
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ተስፋዬ ብዙነህ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዱ ሀሰተኛ መረጃዎችን መመከት ላይ የመገናኛ ብዙሃን ድርሻ ሊጠናከር ይገባል።
ህዝቡን በቀጣናዊ ሁኔታ ላይ ይበልጥ ማስገንዘብ እንደሚገባ ጠቁመው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመከታተልና በማንበብ አቅማቸውን ሊያጎለብቱ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የዲጂታል ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹምእሸት ሽመልስ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙሃን በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና ፖለቲካ መስኮች የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት በማስቀደም በአግባቡ ሊሰሩ ይገባል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከባለድሻ አካላት ጋር በመሆን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ግንዛቤ ለማስፋት ስልጠና ተኮር የውይይት ድረክ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ተቋሙ የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ ሙሳ መሀመድ በሰጠው አስተያየት መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያለንን እይታ እንድናሰፋና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ዘገባ እንድንሰራ የሚያግዝ ነው ብሏል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያዘጋጀው መርሃ ግብር ለሌሎች መገናኛ ብዙሃንም አርአያ የሚሆን ነው ሲልም ተናግሯል።
የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ(ኦ ቢ ኤን) የዜናና ወቅታዊ ጉዳይ ዳይሬክተር በላይ ተሰማ በበኩሉ መድረኩ በዲፕሎማሲው መስክ ሥራችንን ውጤታማ በሆነ መልኩ እንድንከውን የሚያስችል ነው ብሏል።