ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ስምንት ወራት ወደ ተለያዩ ሀገራት ከላከችው ቡና ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
በበጀት ዓመቱ ከቡና 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል።
በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት 169ሺህ ቶን ቡና በመላክ 916 ነጥብ 48 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት እቅድ ተይዞ ነበር።
ከታቀደው በላይ 257ሺህ ቶን ቡና በመላክ 1 ነጥብ 226 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ባለስልጣኑ ገልጿል።
በተገኘው ገቢ 134 በመቶ እንዲሁም በተላከው የቡና መጠን 152 በመቶ የእቅድ አፈጻጸም በማስመዝገብ የላቀ ውጤት መገኘቱን አመልክቷል።
የኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሆኑንም በመረጃው ላይ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት 400ሺህ ቶን ቡና በመላክ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ማቀዷን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።