ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ትሻለች - አምባሳደር ብሩክ መኮንን

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር ያላትን ታሪካዊ የሁለትዮሽ ትብብርና ግንኙነት እንዲጠናከር በቁርጠኝነት ትሰራለች ሲሉ በእንግሊዝ እና ሰሜን አየርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን ገለጹ።

አምባሳደር ብሩክ መኮንን የሹመት ደብዳቤያቸውን ለእንግሊዝ ንጉሥ ቻርልስ ሣልሳዊ በባኪንግሃም ቤተ መንግስት አቅርበዋል።


 

አምባሳደሩ ከእንግሊዙ ንጉስ ጋር በነበራቸው ውይይት በቆይታቸው በሀገራቱ መካከል ያለውን ታሪካዊ እና ዘላቂ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች የበለጠ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የተያዘው ዓመት በሁለቱ ሀገራት ዘላቂ ግንኙነት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የተመዘገበበት የግርማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ዳግማዊ የኢትዮጵያ ጉብኝት 60ኛ ዓመት መሆኑን ጠቅሰዋል።

አምባሳደር ብሩክ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ንጉሥ ቻርልስ ሣልሳዊ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ እንደጋበዟቸውም መልዕክት ማድረሳቸውን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም