አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከቻይና የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከቻይና የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፡- በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከቻይና የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ቼን ሺያኦዶንግ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ውይይታቸው "55 ዓመታት፡ ጠንካራ አጋርነት ለጋራ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ያለውን 55ኛ ዓመት የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በዓልን የተመለከተ እንደነበርም ተገልጿል።
በውይይቱም በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማሳደግ ላይ ሁለቱም ወገኖች አፅንኦት ሰጥተው መወያየታቸውን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በተጨማሪም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ትብብርን ማጠናከር የሚቻልባቸውን መንገዶች ማንሳታቸውም ተጠቅሷል።
ቻይና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት፣ ቀጣናዊ መረጋጋት እና የህዝብ ለህዝብ ግኑኙነት የምታደርገውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍም በተመለከተ ተወያይተዋል።
ሁለቱም ወገኖች በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን ታሪካዊ እና ጠንካራ ግንኙነት ለጋራ ተጠቃሚነት የበለጠ ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን በመረጃው ተመላክቷል።