ቀጥታ፡

ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 5/2017 (ኢዜአ)፦መንግስት ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ስነ ምህዳር ለመፍጠር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሶስትዮሽ ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ የውጭ ባለሀብቶች ምቹ እና ሳቢ የኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።

በስራ ላይ ለሚገኙ ባለሀብቶች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ እና የውጭ ባለሀብቶች ለሚገጥሟቸው ችግሮች ፈጣን ምላሽ መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መክረዋል።

በተደጋጋሚ የኃይል አቅርቦት ችግር በገጠማቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ከባለሀብቶች ጋር ያለውን የትብብር ስራ ለማጠናከር ከስምንት ላይ ተደርሷል።

ኮሚሽኑ በቀጣይነትም ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ፣ አስቻይ እና ግልፅ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ቅንጅታዊ አሰራር እና ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም