ቀጥታ፡

አቶ ጌታቸው ረዳ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች ማብራሪያ ሰጡ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፦የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።


 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የተመሰረተ ግልጽ ኃላፊነትና ህጋዊ ቅቡልነት ያለው አስተዳደር ነው።

ይሁን እንጂ ህጋዊ ተቀባይነት ያጣ አንድ የህወሃት ቡድን ከተወሰኑ የታጣቂ መሪዎች ጋር በመተባበር በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ስልጣን በኃይል ለመንጠቅ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ህዝብና ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በትክክል እንዲተገበር እንደሚፈልጉ ገልጸው፣ ህገወጥ ቡድኑ ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩን በኃይል ለማፍረስ በፈጠረው ችግር የፕሪቶሪያውን ስምምነት በግልጽ ንዶታል ብለዋል።

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተጀመረው ጥረት በዚሁ ቡድን መስተጓጎሉን ገልጸዋል።

በመሆኑም ጊዜያዊ አስተዳደሩን በኃይል በማፍረስ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ገቢራዊ እንዳይሆን እያደረጉ ያሉት ጥቂት የህወሓት እና የታጣቂ አመራሮች መሆናቸውን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግልጽ ሊያውቅ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተሓድሶ ኮሚሽን በፌዴራል መንግስትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የጀመረው እንቅስቃሴ በዚሁ ቡድን መቋረጡንም አብራርተዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የትግራይ ክልልን ወደ ብጥብጥና ትርምስ ያስገባውን ኃይል ለማስቆም አስፈላጊውን ጫና እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም