መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ትላልቅ ህልሞችና ግቦች ላይ ትኩረት ያደረጉ አጀንዳዎችን ቀርጸው ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ትላልቅ ህልሞችና ግቦች ላይ ትኩረት ያደረጉ አጀንዳዎችን ቀርጸው ሊሰሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፦መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ትላልቅ ህልሞችና ግቦች ላይ ትኩረት ያደረጉ አጀንዳዎችን ቀርጸው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩትና ከሆርንቪው ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
መድረኩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በመገንዘብ ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሰሩ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በመድረኩ ከተለያዮ መገናኛ ብዙሃን የተወጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር ) በዚሁ ወቅት በደም በተከፈለ መስዋዕትነት ሉዓላዊነታችንን ብናስከብር በምግብ ራስን መቻልን ጨምሮ በርካታ የቤት ስራዎችም አሉብን ነው ያሉት፡፡
ምርታማነትን በማሳደግ ከጥገኝነት መላቀቅ የአገሪቱ አንዱ ግብ መሆኑን ጠቁመው፥በነዚህና መሰል አጀንዳዎች ላይ የሚሰሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዘላቂ የሰላም ግንባታና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ አጀንዳዎች ላይ በቂ ዝግጅት በማድረግ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ነው ያስታወቁት፡፡