አካዳሚው የተለያዩ የማስተርስ መርኃ ግብሮችን መስጠት ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
አካዳሚው የተለያዩ የማስተርስ መርኃ ግብሮችን መስጠት ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የተለያዩ የማስተርስ መርኃ ግብሮችን መስጠት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ሁለንተናዊ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ አስተማማኝ አቅም ያለው አመራር መፍጠር ወሳኝ ነው፡፡
በዚህ ረገድ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ አህጉራዊ የአመራር ክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት የራሱን ድርሻ ለማበርከት መቋቋሙ ይታወቃል።
ተቋሙ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ሁለንተናዊ ብልጽግና እና መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ አበክሮ እየሰራ ይገኛል፡፡
የአካዳሚው የጠቅላላ አመራር ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ እሸቴ አበበ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት አካዳሚው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ወደ ስራ ገብቷል።
ተቋሙ የተለያዩ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩባቸው 12 ማዕከላትን በመክፈት የሚደረጉ ሙግቶችን ስዋህሊና አረብኛን ጨምሮ በሌሎች ቋንቋዎች ለአፍሪካውያን ወንድሞች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በአካዳሚው የሚሰጡት ፕሮግራሞች አፍሪካን የሚወክሉና የአገራቱን ችግር የሚፈቱ መሆናቸውን አንስተው፥ የአመራር ልማት ስልጠናው ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ በተለያዩ መንገዶች የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
የአካዳሚውን መሰረተ ልማትና የሰው ኃይል አፍሪካዊ ቀለም ለማላበስ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተቋሙ አራት የማስተርስ መርኃ ግብሮችን ለመስጠት መታቀዱን ገልፀው፥አንዱን በመጪው መስከረም ለመጀመር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
አካዳሚው አፍሪካውያንን የሚወክል አጀንዳ በመንደፍ የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካውያን ለመፍታት የሚያስችል መድረክ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ከስልጠና ባለፈ ለውጥ ለሚያስመዘግቡ አፍሪካዊ መሪዎች ሽልማትና እውቅና ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።