ተለዋዋጩን የዓለም ነባራዊ ዐውድ በመገንዘብ የኢትዮጵያን ጥቅም ያስቀደሙ የሚዲያ ስራዎችን መስራት ይጠይቃል - ኢዜአ አማርኛ
ተለዋዋጩን የዓለም ነባራዊ ዐውድ በመገንዘብ የኢትዮጵያን ጥቅም ያስቀደሙ የሚዲያ ስራዎችን መስራት ይጠይቃል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 05/2017(ኢዜአ)፦ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የዓለምን ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስከበሩ ስራዎች ላይ ይበልጥ አተኩረው እንዲሰሩ ተጠየቀ።
ተለዋዋጭ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ እና የጂኦ-ፖለቲካል አሰላለፍ በሚዲያ ስራዎች የሚኖረው አንድምታ ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ተኮር የፓናል ውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
መድረኩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትና ሆርን ሪቪው ከተሰኘ ኦንላይን ሚዲያ ተቋም ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው።
ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት የተወጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉበት መድረኩ፤ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አሁናዊ የዓለም ተለዋዋጭ ዐውድ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ጨብጠው እንዲሰሩ ለማስቻል ያለመ ነው።
የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዲፕሎማት ዘሩባቤል ጌታቸው (ዶ/ር)ን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዮት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በረከት ድሪባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ጥቅም በማስከበር ረገድ ትልቅ የዲፕሎማሲ አቅምን ፈጥራሉ።
ለዚህም የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ፍላጎት መረዳት እንደሚገባ ጠቁመው፤ መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ፋይዳቸው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በመስኩ የመገናኛ ብዙሃንን አቅም የሚያጎለብቱ ስራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የዛሬው መድረክም መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥና ምክክር በማድረግ ግንዛቤን ለማስፋት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የዲጂታል ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹምእሸት ሽመልስ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የዓለምና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ ይዘው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና ፖለቲካ መስኮች የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት ማስቀደም እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከባለድሻ አካላት ጋር በመሆን መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ግንዛቤ ለማስፋት ስልጠና ተኮር የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።