በአማራ ክልል በቀሪ እርጥበት ከለማ መሬት ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በቀሪ እርጥበት ከለማ መሬት ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኘ

ባህር ዳር፤ መጋቢት 5/2017 ( ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል ቀሪ እርጥበትን በመጠቀም በተለያየ ሰብል ከለማ መሬት ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አሰታወቀ።
ምርቱ የተገኘው የክረምቱን መውጣት ተከትሎ በቀሪ እርጥበት ዳግም ከለማው ከ334 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት ላይ መሆኑን ቢሮው ገልጿል።
የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እንዬ አሰፋ፤ በቀሪ እርጥበት የለማው የሰብል ምርት በክልሉ የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ገብስ፣ ስንዴ፣ አጃ፣ ጤፍ፣ ሸምብራ፣ ጓያ፣ ምስር እና ቦሎቄ ሰብል ከለማው መሬት ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት መቻሉን አስታውቀዋል።
ይህም አፈጻጸም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቁመው፤ በልማቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
የዝናቡ መውጫ ወቅት መራዘም ገብስና ስንዴን ጨምሮ ለጥራጥሬ ምርቶች ፍሬ አያያዝ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ለምርቱ መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ወይዘሮ እንዬ አስረድተዋል።
በልማቱ ከተሳተፉት መካከል በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ አርሶ አደር መንግስቴ ዘሩ በሰጡት አስተያየት፤ ቀሪ እርጥበትን ተጠቅመው በጤፍ ካለሙት ግማሽ ሄክታር መሬታቸው ስድስት ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር ነጋ ዋለ በበኩላቸው፤ በግማሽ ሄክታር መሬት በስንዴና ጓያ በማልማት ምርት ማሰባሰባቸውን ገልጸዋል።
በየዓመቱ ከሚያከናውኑት የዳግም ሰብል ልማት ለተጨማሪ ምርት የምግብ ዋስትናቸውን ከመሙላት አልፈው ከምርት ሽያጭ በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አርሶ አደሮች አስታውቀዋል።
የግብርና ቢሮው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በቀሪ እርጥበት ዳግም በሰብል ከለማው መሬት 3 ሚሊዮን 182 ሺህ ኩንታል ምርት ተገኝቷል።