ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ በኮሪደር ልማት ተነሺ ለሆኑ አንቀሳቃሾች የተጀመረው የሼድ ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ ነው

ጎንደር፤መጋቢት 5/2017 (ኢዜአ)፦በጎንደር ከተማ አስተዳደር በኮሪደር ልማት ከሥራ ቦታቸው የተነሱ አንቀሳቃሾችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የሼድ ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በኮሪደር ልማት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ለዚህም በልማቱ ከመስሪያ ቦታቸው የተነሱና ቁጥራቸው 2 ሺህ የሚጠጉ ተነሺዎችን ለማስተናድ የሚያስችሉ የአራት ሼዶች ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸው ቦታ ላይ እየተገነቡ ያሉ ሼዶች ለማምረቻና ለመሸጫ አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የሁለቱ ሼዶች አፈጻጸም 65 በመቶ መድረሱን ጠቁመው፣በተያዘው ዓመት አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ በጠንካራ ክትትል ይሰራል ብለዋል።

የጥቃቅን አንቀሳቃሽ ተነሺዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማቋቋም ወደ ሥራ ለማስገባት እንዲቻል በከተማ አስተዳደሩ ወጪ ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ አበዳሪ ተቋማት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በከተማው የፒያሳ እና አካባቢው የኮሪደር ልማት ሥራ በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባዋ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማትም በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በኮሪደር ልማቱ ህብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት እየተሳተፈ መሆኑን ጠቁመው፣ የልማት ሥራው ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አስረድተዋል።

ከፒያሳ- አዘዞ- አየር ማረፊያ የሚዘልቀው ሁለተኛው የኮሪደር ልማት የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን ጨምሮ የአረንጓዴ መናፈሻና የአስፋልት ጥገና ሥራዎችን አካቶ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም