ቀጥታ፡

የአካባቢውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያቀላጥፈው የላሊበላ-ኩልመስክ-ሙጃ መንገድ ፕሮጀክት እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦ 48 ነጥብ 78 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የላሊበላ-ኩልመስክ-ሙጃ የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ፕሮጀክት በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡

በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ የዲዛይን፣ የአፈር ጠረጋ፣ የቆረጣ፣ የሙሌት፣ የውሃ ማፋሰሻ ቱቦ ቀበራ፣ የሰብ ቤዝ ሥራዎች እንዲሁም የድልድይ ግንባታን ጨምሮ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገልጿል፡፡

ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ዓለም አቀፉቻይና ሲቪል ኢንጂነሪነግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሲሆን የማማከሩንና የቁጥጥሩን ሥራ ቤዛ ኢንጅነሪንግ ኬኒያ ሊሚትድ እያከናወነ መሆኑም ተመላክቷል፡፡


 

የመንገዱ አጠቃላይ የጎን ስፋት በገጠር 8-10 ሜትር፣ በቀበሌ 16 ሜትር እንዲሁም በወረዳ 20 ነጭብ 5ሜትር ስፋት ያለው መሆኑም ተገልጿል፡፡

ለግንባታ የሚውለው 1,888,292,297 (አንድ ቢሊየን ስምንት መቶ ሰማንያ ስምንት ሚሊዮን ሁለት መቶ ዘጠና ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ሰባት ብር) በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ የተደረገ ነው፡፡

የአትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከአካባቢው አስተዳደር እና ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረጉ አሁን ላይ የተሻለ የፕሮጀክት አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡


 

መንገዱ ሲጠናቀቅ በዋናነት የላሊበላ፣ የኩልመስክ እና የሙጃ ከተሞችን በቅርበት የሚያስተሳስር ሲሆን ወደ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያናት መዳረሻ በመሆን ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እንደሚያግዝም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በአካባቢው የሚመረቱ እንደ ዘንጋዳ፣ ገብስባቄላ እና ሌሎች የግብርና ውጤቶችን ወደ ገበያ በቀላሉ ለማድረስ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የአካባቢውን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ እንቀስቃሴ ያፋጥናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም