ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በብራዚል እየተካሄደ በሚገኘው የብሪክስ የግብርና ጉዳዮች መድረክ ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በብራዚል ዋና ከተማ ብራዚሊያ እየተካሄደ በሚገኘው የብሪክስ የግብርና ጉዳዮች መድረክ ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች።

መድረኩ እአአ ከማርች 12 እስከ 14/2025 ለሶስት ቀናት ይቆያል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ልዑክ ኢትዮጵያ በግብርና ልማት፣ በምግብ ዋስትና እና በቤተሰብ ደረጃ እየተገበረች ያለውን የግብርና ፕሮግራም በተመለከተ ማብራሪያ በመስጠት ልምድ አጋርቷል።


 

በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ሰጥታ በትኩረት እየሰራችባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በተጨማሪም ከፍተኛ ውጤት የተገኘባቸውን እንደ ብሄራዊ የስንዴ ልማትና የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ የተቀናጀ የግብርና ልማትን፣ የምግብ ዋስትናንና የስርዓተ ምግብ ፕሮግራም ትግበራን አጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል።


 

አምባሳደር ልዑልሰገድ አክለውም ኢትዮጵያ በርሃማነትን መከላከል፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥና የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ነድፋ እየተገበረች እንደምትገኝ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላከታል።

በብሪክስ ማዕቀፍ በግብርና ልማት ዘርፍ ያሉ ልምዶች ለመለዋወጥ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንበታ እና በዘርፉ ኢንቨስትመንት ማስፋፋት አንዱ የትብብር ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።


 

የብራዚል የግብርና ልማት ሚኒስትር ፓውሎ ቴይዜራ በበኩላቸው በብሪክስ ማዕቀፍ በግብርና ዘርፍ ትብብርን ማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ማንሳታቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም