ቀጥታ፡

ባለሃብቶች ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ሥርዓት ተወዳዳሪነት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት ተዋናዮች ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ሥርዓት ተወዳዳሪነት እራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ የኤግዚቢሽን ማዕከል የተዘጋጀውን የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት መርቀው ከፍተዋል።

የኢትዮጵያን ይግዙ በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው 14ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከዛሬ መጋቢት 04 እስከ 8/2017 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ የሚያስችሉ የፖሊሲ ማሻሻ እርምጃዎች ተወስደዋል ብዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶችም ሀገራዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ይግዙ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትም የንግዱን ማህበረሰብና ሸማቹን በማስተሳሰር ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት መነቃቃት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ ገበያውን ለውጭ ጅምላና ችርቻሮ፤ አስመጪና ላኪዎች ክፍት በማድረግ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን አንስተዋል።

የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃም የወጪ ንግድ ገቢን አሳድጓል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሰባት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች ከ3 ነጥብ 8 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

ለገቢ መገኘትም ወርቅ፣ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ኤሌክትሪክና የቁም እንስሳት ንግድ የአንበሳውን ድርሻ እንደተወጡ አስረድተዋል።

በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ እና የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን ለመቀላቀል በሚደረገው ዝግጅት አምራቾች የንግድና ኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሰብስብ አባፊራ፤ በኢትዮጵያ ዕድገት ላይ የመሪነት ሚና የሚጫወት የንግድና ኢንቨስትመንት ሥርዓት እንዲፈጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የግሉን ዘርፍ የልማት እንቅስቃሴ ለመደገፍ ተግባራዊ የተደረጉ የፖሊሲ እርምጃዎች ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ የንግድ ትርዒት የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ለኢንዳስትሪ ልማት ዕድገት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና የገበያ ትስስር ገንቢ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር ያዘጋጁት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ አምራቾች ምርትና አገልግሎታቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም