ኢዜአ የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አክብረዋል።
ቀኑ "ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል" በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት የሴቶችን ተሳትፎና ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።
በተለይም በሰላምና ልማት ግንባታ ስራዎች የጎላ ሚና ያላቸው በመሆኑ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው፤ የተቋሙ ሴት ባለሙያዎችም በሁሉም ዘረፍ ተወዳዳሪነታቸውን ይበልጥ ለማጎልበት መትጋት አለባቸው ብለዋል።
በተቋሙ የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር ወይዘሮ ታደለች ቦጋለ በበኩላቸው የሴቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የሀገር ውስጥና የውጭ የትምህርት እድሎች ጨምሮ የስራ እድገት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል ጋዜጠኛ ብዙአየሁ ቦጋለ እንዳለችው የሴቶችን ተሳትፎና እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው።
ጋዜጠኛ ሃናን ጀይላን ሴቶች ጊዜው ከሚፈልገው አሰራር ጋር ራሳቸውን በማብቃት በስራቸው ይበልጥ ውጤታማ መሆን ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ነው በአስተያየታቸው የገለጹት።
ኢዜአ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራው ባለው ስራ የትምህርት እድል በማግኘት ተጠቃሚ መሆኗን የገለጸችው ደግሞ ወይዘሪት ሳራ ተክሉ ነች።