ቀጥታ፡

የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ስራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦ ሀገር አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነች ላለው ስራ ድጋፍ እንዲያደርጉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

ሚኒስቴሩ ከፋይናንስ ተቋማት አመራሮች ጋር ዛሬ ውይይት አድርጓል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፥መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚያስችሉ ተጨባጭ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ፥ የሌማት ትሩፋትና የበጋ ስንዴ ምርት ውጤታማ ስራ ከተከናወነባቸው ዘርፎች መካከል ዋንኞቹ እንደሆኑ አንስተዋል።

የታዳሽ ኃይል የማስፋት ስራ፣ ዘላቂ መሬት አጠቃቀም እና የኮሪደር ልማት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋትና አረንጓዴ ልማት ለማረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየችበት ነው ብለዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ ላይ ተሳትፎ ለሚያደርጉ የፋይናንስ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

የፋይናንስ ተቋማት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ተጋላጭ በመሆናቸው ያላቸውን ሃብትና እውቀት በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት በማድረግ እንዲሳተፉ መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራ፣ ድጋፍም ያደርጋል ብለዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ ስዩም መኮንን፥ የሀገር ውስጥ ፋይናንስ ተቋማት ከዓለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር ለአረንጓዴ ልማት ወይም አየር ንብረት ለውጥ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የፋይናንስ ተቋማቱም በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ አስተዋጽኦ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በውይይቱ ላይ መግለጻቸውን ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም