ቀጥታ፡

ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚውል ድጋፍ ህዝቡን በማስተባበር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

ሰቆጣ፤ መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፡- በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር  ለታላቁ የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ ግንባታ  የሚውል ድጋፍ ህዝቡን በማስተባበር ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል የብሔረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ ገለጹ። 

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ለህዳሴው ግድብ ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ ለማሰባሰብ የቦንድ ሽያጭ መርሃ ግብር ዛሬ በሰቆጣ ከተማ ተጀምሯል። 

የቦንድ ሽያጩ   በ15 ቀናት ውስጥ እንደሚከናወን  ተመልክቷል። 

ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪው በወቅቱ እንደገለጹት፤የአስተዳደሩ ህዝብ ባለፉት ዓመታት  ቦንድ በመግዛት ግድቡ አሁን ከደረሰበት ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ እንዲገኝ የበኩሉን  አስተዋጽኦ አበረክቷል፤  አስተዳደሩም የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል።


 

ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በአመራሩ ዛሬ የተጀመረውን የቦንድ ግዥ በቀጣይ ወደ ህዝቡ በማውረድ የታቀደውን የሁለት ሚሊየን ብር ቦንድ ግዥ ለማሳካት እንደሚሰራ አስታውቀዋል። 

ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ህብረተሰቡም   ቦንድ በመግዛት የዜግነት ግዴታውን  እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ከፍያለው ማለፉ በበኩላቸው፤  ለ6ኛ ጊዜ የቦንድ ግዥ በመፈጸም  የህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ የልማት ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።


 

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ፍትሃለሽ ምህረቴ ፤ ለ4ኛ ጊዜ ቦንድ ግዥ በመፈጸም  ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ የበኩላቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል። 

ቄስ አዳነ አዲሱ በበኩላቸው፤ ለህዳሴው ግድብ ቦንድ በመግዛት በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም