ኢትዮጵያ ከኩባ ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት አላት- አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከኩባ ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት አላት- አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከኩባ ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት እንዳላት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
አፈ-ጉባዔው በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ሜይሊን ሱዋሬዝ አልቫሬዝ ከተመራ ልዑካን ቡድን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይቱ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ወዳጅነትን ማጠናከር ያለመ ነው።
ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና ኩባ ጠንካራ ወዳጅነት ያወሱት አፈ-ጉባኤው፥ ኩባ ለኢትዮጵያ በትምህርት፣ በጤና እና በወታደራዊ ዘርፍ ላደረገችው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የሀገራቱን ታሪካዊ የወዳጅነት ግንኙነት በፓርላማ ዲፕሎማሲ እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ረገድ የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ጽኑ ፍላጎት አላት ብለዋል።
የኩባ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እና በልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ሜይሊን ሱዋሬዝ አልቫሬዝ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ጠንካራና ታሪካዊ መሆኑን አንስተዋል።
ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የወዳጅነት ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ እና ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1976 እንደጀመሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።