ቀጥታ፡

ሀገር-አቀፍ የቁርአን ሂፍዝ የማጣሪያ ውድድር ተካሄደ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ሀገር-አቀፍ የቁርአን ሂፍዝ የማጣሪያ ውድድር ዛሬ ተካሄዷል።

የቁርአን ሒፍዝ ውድድሩ ሴቶችንና ወንዶችን ያካተተ ሲሆን ተወዳዳሪዎቹ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ ናቸው።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፉ፥ ውድድሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፤ ቁርአን የሰላም መንገድ ነው፡፡

ለዚህም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው ሀገር-አቀፍ የቁርአን ሂፍዝ ውድድር "ቁርአን የእውቀትና የሰላም ምንጭ" በሚል መሪ ሃሳብ እንዲከናወን መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ለመማር፣ለማምለክ፣ ለመስራት እና ወጥቶ ለመግባት ሰላም በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ለሀገር ዘላቂ ሰላም ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኡስታዝ አቡበክር አሕመድ በበኩላቸው፥ውድድሩ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የኡለማ ምክር ቤት ትብብር ነው ብለዋል።

የማጠቃለያ ውድድሩ የፊታችን እሁድ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚከናወን አመላክተዋል፡፡

የውድድር መርሃ ግብሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም