ቀጥታ፡

የፌደራል መንግሥት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት በራሱ ተሳትፎ የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የገጠመውን አደጋ የመቀልበስ ኃላፊነት አለበት- አቶ ጌታቸው ረዳ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦የፌደራል መንግሥት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት በራሱ ተሳትፎ የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የገጠመውን አደጋ የመቀልበስ ኃላፊነት እንዳለበት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ በመግለጫቸው፣ የትግራይ ህዝብ ሰላም አብዝቶ የሚፈልግና የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ከምርጫ ቦርድ እውቅና ውጭ ጉባኤ አካሂጃለሁ የሚለው የህግ ተቀባይነት የሌለው የህወሓት አንድ ቡድን ክልሉ ላይ አደጋ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ዋና ዓላማ ተኩስ ማቆም እና አንድ የመከላከያ ሰራዊት መገንባት መሆኑን ገልጸው፥የፌደራል መንግስቱ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚያደርገውን ድጋፍ ማጠናከር አለበት ብለዋል።

በዚህም የፌዴራል መንግስት ትግራይ ክልል ውስጥ ባሉ የፌደራል ተቋማት አማካኝነት የትርምሱ አካል የሆኑ አካላት ላይ ህጋዊ አካሄድን የተከተለ የእርምት እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በትግራይ ክልል የግለሰቦችን ስልጣን ለማስጠበቅ የሚዋጋ ወጣት እንደማይኖርም ተናግረዋል።

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ተፈናቃዮችን የመመለስ እና የታጣቂዎችን መልሶ ማቋቋም ሂደትም የተስተጓጎለው በራሳችን የውስጥ ሽኩቻ ነው ብለዋል።

ለአብነት ከፌደራል መንግስት በዛሬው እለት በመልሶ ማቋቋም የሚካተቱ ታጣቂዎችን ለማቋቋም ወደ መቀሌ የሚሄድ ቡድን እንደነበር አንስተው፣ በራሳችን አካሄድና ትርምስ በተፈጠረ ችግር መሄድ እንዳልቻለም አንስተዋል።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በልኩ ገቢራዊ እንዳይሆን ያደረገው በዋናነት በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሰው ቡድን መሆኑንም ተናግረዋል።

የፌደራል መንግስት የሰራቸውን በጎ ነገሮች መጥቀስ በህገወጡ ኃይል ዘንድ የሚያስወግዝ ሆኗልም ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ ጦርነት የመሸከም አቅም የለውም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ቡድኑ በክልሉ ማህተም ወደ መንጠቅ እና መሬት መሸንሸን ውንብድና ገብቷል ብለዋል።

በክልሉ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህገወጥ የወርቅ ንግድና ሌሎች ህገወጥ እንቅስቃሴዎች ለክልሉ ሰላም መደፍረስ አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም