ቀጥታ፡

ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት ያስመዘገበውን ስኬት አጠናክሮ መቀጠል አለበት

አዲስ አበባ፤መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባለፉት ስድስት ወራት ያስመዘገበውን ስኬት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አስገነዘበ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤልን ጨምሮ የተቋሙ ሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ምልከታ አድርገዋል።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት በገቢና የወጪ ንግድ ጭነት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሰዋል።

ከሚሰጣቸው አገልግሎቶችም በግማሽ ዓመቱ ከ46 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጸው፤ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

በዚህም ተቋሙ ከታክስ በፊት 6 ቢሊየን ብር ለማትረፍ አቅዶ 9 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን ጠቅሰዋል።

ተቋሙ ይህን ውጤት ለማስመዝገብ የቻለው የመዳረሻ ሀገራትን በማስፋትና የአፍሪካን ገበያ በአግባቡ በመጠቀም ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ኃይለ ሚካኤል የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የተሰማራበት ዘርፍ በዓላም ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ነው ብለዋል።

ይህም ከፍተኛ የሆነ የዓለም የጭነትና የንግድ ባህር ትራንስፖርት የሚከናወንበት እንዲሁም ከፍተኛ ፋይናንስ የሚንቀሳቀስበት እንደሆነም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በዚህ የዓለም ሁኔታ ውስጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት በገቢ እና ትርፍ ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገልፀው፤ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።

ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት ያስመዘገበውን ስኬት በቀጣይ ወራትም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም