ህብረተሰቡ የደም ልገሳን ባህል በማሳደግ በህይወት አድን ተግባር ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ የደም ልገሳን ባህል በማሳደግ በህይወት አድን ተግባር ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ
አዳማ ፤መጋቢት 4/2017 (ኢዜአ)፡-ህብረተሰቡ የደም ልገሳን ባህል በማሳደግ በህይወት አድን ተግባር ላይ እንዲሳተፍ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።
አገልግሎቱ ከኃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና ሀደ ስንቄዎች ጋር በደምና ሕብረ ህዋስ ዙሪያ ለመምከር ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ በአዳማ ተካሄዷል።
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በወቅቱ እንዳሉት ደምና የዓይን ብሌን ከሰው ብቻ የሚገኝ አካል በመሆኑ ህብረተሰቡ በበጎ ፈቃደኝነት የሚያደርገውን ልገሳ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
አገልግሎቱ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ፈጥኖ ለማድረስ እያደረገ ባለው ጥረት በቀን 1 ሺህ 100 ዩኒት ደም እየሰበሰበ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ አሃዝ በቀን ከሚያስፈልገው ከ2 ሺህ 500 እስከ 3 ሺህ 500 ዩኒት ደም ጋር ሲነፃጸር ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህንን ተግዳሮት ለማቃለል መላው ህብረተሰብ የደም ልገሳ ባህሉን በማጠናከር በህይወት አድን ተግባሩ ላይ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።
በዚህ ረገድም የኃይማኖት አባቶች፣ የአባገዳዎችንና የሀደ ሲንቄዎችን ሚና ለማጎልበት ታስቦ መድረኩ መሰናዳቱን አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ከበጎ ፈቃደኞች 500 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ በመጀመሪያዎቹ ሰባት ወራት 243 ሺህ ዩኒት ደም ተሰብስቦ ለህክምና ተቋማት መሰራጨቱን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የጾም ወቅት መሆኑን ተከትሎ የደም ዕጥረት እንዳይከሰት ምእመናኑን ያሳተፈ የደም ልገሳ መርሃ ግብር በየደረጃው እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
ለዚህም ሰፊ የቅስቀሳና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ ነው ዳይሬክተሩ ያመላከቱት።
በመሆኑም ደም የማይሸጥና የማይለወጥ ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ተሰብስቦ ለጤና ተቋማት በነፃ የሚቀርብ መሆኑን በመገንዘብ ህብረተሰቡ ደም በመለገስ የሰዎችን ህይወት የማዳን ሰብዓዊ ግዴታውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌልና የሸገር ከተማ የኃይማኖት ተቋማት ሰብሳቢ መልአከ ኃይል አባ አፈወርቅ ዮሐንስ በሰጡት አስተያየት ደም ልገሳ የህይወት ስጦታ መሆኑን በመረዳት ሁላችንም ደም ልገሳን ባህላችን ልናደርግ ይገባል ብለዋል።
በዓብይ ፆም ወቅት ደም መለገስ ከመልካም ስራዎች አንዱ በመሆኑ እፎይታን እንደሚሰጥ ጠቅሰው ቤተክርስቲያኗም ህዝበ ክርስቲያኑ በልገሳው በነቂስ እንዲሳተፍ በየአድባራቱ አጀንዳ ይዛ እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል።
ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ የአዳማ ከተማ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ሼህ አብዱልቃድር ሼህ አህመድ በበኩላቸው ደም ልገሳ ከሚሰጠው እርካታ ባሻገር የራስንም ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በረመዳን ወርም ደም መለገስ እንደ መልካም ሥራ ስለሚቆጠር በደም ምክንያት የሰው ሕይወት እንዳይቀጠፍ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ይገባናል በማለት ለዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራን ነው ብለዋል።