ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሰባት ወራት ከወጪ ንግድ ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦በ2017 በጀት ዓመት ሰባት ወራት ከወጪ ንግድ ከ3 ነጥብ 8 ቢሊየን በላይ የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የኤግዚቢሽን ማዕከል የተዘጋጀውን የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት መርቀው ከፍተዋል።

በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የሀገራት አምባሳደሮች፣ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የምርትና አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

"የኢትዮጵያን ይግዙ" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው 14ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከዛሬ መጋቢት 04 እስከ 8/2017 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌትነትን ለማረጋገጥ ሰፋፊ የንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅድ ተቀርፆ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ወደስራ በማስገባት በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት በመገንባት ስኬታማ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት ከወጪ ንግድ ከ3 ነጥብ 8 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።

የወርቅ እና ቡና ምርቶችን ጨምሮ ግብርና፣ ማዕድንና የኢንዱስትሪ ምርትና አገልግሎቶች ከፍተኛውን ድርሻ እንደያዙ ገልጸዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት አባልነት ሰፋፊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ አምራቾች የንግድና ኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ፥ ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ለአንድ ሀገር ዕድገት መሰረቶች ናቸው ብለዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የመሪነት ሚና ያለው የንግድና ከባቢ ለመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ምክርቤቱ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተሰናዳው የንግድ ትርዒት የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች በማስፋፋት የገበያ ትስስርን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከተባባሪ አካላት ጋር ያዘጋጁት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ የሀገር ውስጥ፣ የአፍሪካ ሀገራትና የዓለም አቀፍ አምራች ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን አቅርበዋል።

ዓለም አቀፉ የንግድ ትርዒትም የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶች በማስተዋወቅ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችን የገበያ ትስስር፣ የዕውቀትና የልምድ ልውውጥ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህም በሀገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞችና በዓለም ዓቀፍ የንግድ ተቋማት ምርትና አገልግሎቶች ቀርበው የአቻ ለአቻ የንግድ የምክክር መድረክ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም