የኢትዮጵያን የስርዓተ ምግብ ሽግግር ለማሳካት የሚደረገውን ጥረትና ተሞክሮ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የስርዓተ ምግብ ሽግግር ለማሳካት የሚደረገውን ጥረትና ተሞክሮ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዳማ፤መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የስርዓተ ምግብ ሽግግር ለማሳካት የሚደረገውን ጥረትና ተሞክሮ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለውን ጥረት ታሳቢ በማድረግ የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ምግብ ጉባኤን እንድታዘጋጅ መመረጧ ይታወቃል።
ጉባኤው እ.ኤ.አ ከሐምሌ 27 እስከ 29 ቀን 2025 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ዝግጅት እየተደረገም ይገኛል።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት እያከናወነች ባለው ተግባር ዙሪያ ተሞክሮዋን ለዓለም ማህበረሰብ ለማስገንዘብ በሚቻልበት ሂደት ላይ በአዳማ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ስርዓተ ምግብር ሽግግርና ኒውትሪሽን ዋና አስተባባሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ይህ ጥረትና ተሞክሮዋ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኘ በመሆኑ ለሌሎች ማጋራት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል ነው ያሉት።
በተለይም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምግቦችን ማምረት፣ የፖሊሲና አሰራር መፍትሄዎችን ማበጀት፣ ቴክኖሎጂን ወደ ግብርና ኢንዱስትሪ በስፋትና በብዛት እንዲገባ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የንግድ ትስስርና የእሴት ሰንሰለትን በመዘርጋት የድህረ ምርት ብክነትን ማስቀረት፣ የአደጋ ተጋላጭነትን መቀነስ፣ በገጠራማው አካባቢ የሃይል አቅርቦትና የስራ ክህሎት ስልጠናን ተደራሽ ማድረግ በትኩረት መከናወናቸውንም አስረድተዋል።
ከዚህም በመነሳት የስርዓተ ምግብ ሽግግር ለማሳካት የሚደረገውን ጥረትና ተሞክሮ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የግብዓት አቅርቦት መሪ ስራ አስፈፃሚ መንግስቱ ተስፋ፤ ኢትዮጵያ ስርአተ ምግብን ለማሻሻል እያከናወነች ያለውን ጥረት በተመለከተ ተሞክሮዋን ለጉባኤው ለማቅረብ መመረጧን አስታውሰው ለዚህም ከወዲሁ ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ይበልጥ ለማስፋት፣ በአረንጓዴ አሻራና የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የስራ ባህልን ለመለወጥና የግብርና ዘርፉን ለማዘመን ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ከሐምሌ 27 እስከ 29 ቀን 2025 ዓ.ም በሚካሄደው ጉባኤ የ160 አገራት ተወካዮች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።