ቀጥታ፡

የኢንስቲትዩት መቋቋም ይባክን የነበረውን የአገር ሃብት የሚያስቀርና የሂሳብ ሪፖርቶች ወጥና ተዓማኒ እንዲሆኑ የሚያግዝ ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋም ይባክን የነበረውን የአገር ሃብት የሚያስቀርና የሂሳብ ሪፖርቶች ወጥና ተዓማኒ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 19ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

በዚሁ ጊዜ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የፋይናንስ ሙያ በአለምአቀፍ ደረጃ ተመሳሳይነት ያለውና ሁሉንም የሚያግባባ ነው ብለዋል።

የኢንስቲትዩቱ መቋቋም የመንግስትና የግል ድርጅቶች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ የተሟላ፣ግልጽ እና በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት መዘርጋት ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሃብት በአግባቡ ለማወቅና በከፍተኛ ወጪ ከውጭ አገር የሚመጣውን ባለሙያ ማስቀረትና የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚያስችልም ነው ያብራሩት።

እንደ ዶክተር እዮብ ገለጻ፣ የኢንስቲትዩቱ መቋቋም የፋይናንስ ስርዓቱን በማዘመን ይባክን የነበረውን ሃብት ማስቀረትና 10 በመቶ አገራዊ ገቢን ማሳደግ ያስችላል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ጨምሮ የካፒታል ገበያን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሏትን የህግ ማዕቀፎች ማውጣቷን አስታውሰዋል።

እነዚህን ስምምነቶች በአግባቡ ለመተግበር ውጤታማና በአለምአቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው የሂሳብ ባለሙያዎቸን በብዛትና በጥራት ማፍራት ይገባል ብለዋል።

አለምአቀፍ ዕውቅና ያለው የሂሳብ ባለሙያ ለመሆን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚጠይቅ ያነሱት አባላቱ በዚህም አገሪቷ አለምአቀፍ ተቀባይነት ያለው ባለሙያ ማፍራት እንዳትችል ሆናለች ብለዋል።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋም ለችግሮቹ መፍትሄ መሆኑን በማንሳት።

በምክር ቤቱ የፕላን፣ልማትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ የረቂቅ አዋጁን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ አለም አቀፍ ከሆኑ የሙያ ማኅበራት ትምህርታቸውን አጠናቀው በቂ ዕውቀት በመጨበጥ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ጥቂት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ ባለሙያዎቹ የሚያወጡት የሂሳብ ሪፖርት ለግብር ስወራ የተመቸ በመሆኑ አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ ማድረጉን አመልክተዋል።

ኢንስቲትዩቱ የሒሳብ ሙያን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስድና ሀገሪቱ ያለችበትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች ታሳቢ ያደረገ የሒሳብ ባለሙያ ለማፍራት እንደሚያስችል ነው የገለጹት።

የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎ የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት በቅርቡ ይቋቋማል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም