ኢትዮጵያና ቻይና ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ በጋራ መተባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ፈጥረዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ቻይና ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ በጋራ መተባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ፈጥረዋል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያና ቻይና ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ በጋራ መተማመን፣ በመከባበር እና በመተባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፍጠራቸውን በቻይና የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈራ ደርበው ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሰረተበት 55ኛ ዓመት "55 ዓመታት ጠንካራ አጋርነት ለጋራ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በድምቀት ተከብሯል።
በቻይና የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈራ ደርበው ኢትዮጵያና ቻይና ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ በጋራ መተማመን፣በመከባበር እና በመተባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደር ተፈራ የአዲስ አበባ -ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት እና የተለያዩ የሀይል ማመንጫ ጅምር ፕሮጀክቶችን በማውሳት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ትብብር በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ቼን ሺያኦዶንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው የቻይና አጋሮች አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፥ ትብብራቸው ወደ “All-Weather Strategic Partnership” ማደጉን አመላክተዋል።
አያይዘውም ቻይና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ያረጋገጡ ሲሆን፣ በተለያዩ ዘርፎች ዘላቂነት ያለው ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ኢምባሲ በተካሄደው በዚህ ዝግጅት የሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ የቢዝነስ ሃላፊዎች፣ የሚዲያ መሪዎች፣ የዳያስፖራ አባላት እና ተማሪዎች መገኘታቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡