ኢትዮጵያ እና እስራኤል የኢኮኖሚ ትስስራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና እስራኤል የኢኮኖሚ ትስስራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና እስራኤል የጋራ ጥቅም ላይ በመመስረት የኢኮኖሚ ትስስራቸውን የበለጠ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ከእስራኤል የኢኮኖሚ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ኒር ባርካት ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትብብር ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች የሀገራቱን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር እና በሁለቱ ሀገራት የንግድ ማህበረሰብ መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ አጋርነት ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የሁለትዮሽ ውይይቱ ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው የሚገኙ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች እና ቁልፍ የኢንቨስትመንት እድሎች በግልጽ ያመላከተችበት እንደሆነ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ኢኖቬሽን መር በሆኑ የግብርና፣ የቴክኖሎጂ፣ የውሃ አስተዳደር፣ የታዳሽ ኃይል እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች አቅም እንዳላት በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዊስ(ዶ/ር) ለኒር ባርካት ኢትዮጵያ የንግድ ስራ ምቹነትን ለማሻሻል እና የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ እያከናወነች የምትገኝውን የሪፎርም ስራ አስመልክቶ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ሚኒስትሩ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የኢትዮጵያን የልማት አቅጣጫ ከአንድ ዘርፍ ጥገኝነት ወደ ባለብዝሃ የእድገት ምስሶዎች ያሸጋገረ ማዕቀፍ መሆኑን አመልክተዋል።
የመንግስት የኢንቨስትመንት ክንፍ የሆነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽኑ ስትራቴጂያዊ ሚናውን እየተወጣ ነውም ብለዋል።
ሚኒስትር ኒር ባርካት እስራኤል ተወዳዳሪ የሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ስኬታማ ተምሳሌት የሆነች ሀገር ናት ብለዋል።
እስራኤል የግብርና እና ምግብ ቴክኖሎጂ፣ በቴክኖሎጂ የበለጸጉ ኢንዱስትሪዎች፣ በሳይንስ፣ በጤና ክብካቤ እና ዘመናዊ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ጨምሮ በሌሎች ቁልፍ መስኮች ያላትን እድገት በማሳያነት ጠቅሰዋል።
እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር የጋራ ፍላጎቷ በሆኑ መስኮች በትብብር ለመስራት እንደምትሻ ገልጸዋል።
የእስራኤል የንግድ ተቋማት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት አቅም እንዳለም አንስተዋል።
ሁለቱ ወገኖች የኢኮኖሚ ትስስራቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩ የአሰራር ማዕቀፎችን ለመዘርጋት፣ የቢዝነስ ትስስራቸውን ለማጠናከር እና አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለመቃኘት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ሚኒስትሮቹ ዘላቂ እድገትን የሚያረጋግጥ፣ የእውቀት ሽግግርን የሚያሳልጥ እና የጋራ ብልጽግናን የሚፈጥር ውጤታማ ትብብር መፍጠር እንደሚገባም አመልክተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳዓር ጋር በሁለትዮሽ ሀገራዊ እና የባለብዙ ወገን የጋራ ጉዳዮች ላይ ትናንት መወያየታቸው የሚታወስ ነው።