በሆሳዕና ከተማ ከ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

ሆሳዕና፤ መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፡- በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች የሚመልሱ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስተዳደሩ ገለጸ።

በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች የባለሀብቱና የነዋሪው ተሳትፎ የላቀ መሆኑም ተመላክቷል።

የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ ለኢዜአ እንደገለጹት ሆሳዕና ከተማን ምቹና ተወዳዳሪ ለማድረግ ባለሀብቱና ነዋሪውን በማሳተፍ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም የኮሪደር ልማት፣ የአስፓልት መንገድ፣ የጎርፍ ማፋሰሻዎች፣ የከተማ ውበት ሥራዎች፣ መዝናኛና ፓርኮች፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ከ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መሰረተ ልማቶቹ የከተማዋን ተወዳዳሪነትና ተመራጭነት የሚያሳደጉና የነዋሪውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ጥያቄዎች የሚመልሱ መሆናቸውን ጠቅሰው በልማት ሥራው የማህበረሰቡ ተሳተፎ የላቀ ነው ብለዋል።

በቅርቡ ለፕሮጀክቶቹ ማጠናቀቂያ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብር የንግዱ ማህበረሰብ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ለመለገስ ቃል መገባቱንም ተናግረዋል፡፡

የነዋሪውን የልማት ጥያቄ ለመመለስና ከተማዋን ተወዳዳሪና ተመራጭ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎች እንደሚጠናከሩ የገለጹት ከንቲባው ይህን ለማሳካት ገቢን በአግባቡ የመሰብሰብ ሥራው ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡም ለልማቱ በተለያየ መንገድ ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ ለሚፈጽመው ግብይት ደረሰኝ በመቀበል የበኩሉን እገዛ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሆሳዕና ከተማ ተስፋ ሰጪ የልማት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የተናገሩት ደግሞ በከተማዋ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አየለ ኤርቃሎ ናቸው።

መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ማድረግ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፣ ልማቱን ለማጠናከር የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድርጋቸውን ገልጸዋል።

በከተማው በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩት ወይዘሮ አለምፀሐይ ሰብለወርቅ በበኩላቸው አሁን ላይ አስተዳደሩ ነዋሪውን በማሳተፍ እያከናወናቸው ያሉ የልማት ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል፡፡

የልማት ሥራውን በመደገፍ የታሪክ ተጋሪ መሆን ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ አለምፀሐይ ለልማቱ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

ዛሬ የምንሰራው ልማት ለትውልድ የሚተርፍ በመሆኑ ሁላችንም በምንችለው ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም