ቀጥታ፡

የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበርን ጨምሮ አዲስ ተመራጮች ስልጣናቸውን በይፋ ተረከቡ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2017 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ተመራጩ ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍን ጨምሮ ከተሰናባች የኮሚሽኑ አመራሮች ዛሬ ይፋዊ የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።

የርክክብ ስነ ስርዓቱ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተደርጓል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የአንጎላ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ጆአዎ ሎሬንሶ፣ ተሰናባች እና አዲስ የህብረቱ ኮሚሽን አመራሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ "የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ለዘርዓ አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ የካቲት 9 እና 10 ቀን 2017 ዓ.ም በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል።

የመሪዎች ጉባዔው የጅቡቲው ማህሙድ አሊ የሱፍ አዲሱ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እና አልጄሪያዊቷን አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲን የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመበር አድርጎ መምረጡ ይታወቃል።

ማህሙድ አሊ የሱፍ ከሙሳ ፋቂ ማህማት፣ አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ ከሞኒክ ንሳንዛባግዋ (ዶ/ር) ስልጣናቸውን ተረክበዋል።

በተጨማሪም ጉባዔው የሕብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብስባ የመረጣቸውን ኮሚሽነሮች ውጤት ማጽደቁ ይታወቃል።

የሌሴቶው ሞሰስ ቪላካቲ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር፣ ደቡብ አፍሪካዊቷ ሌራቶ ማታቦጅ የኮሚሽኑ የመሰረተ ልማት እና ኢነርጂ ኮሚሽነር እና ጋናዊቷ አምባሳደር አማ ቱም-አሞሃ የኮሚሽኑ የጤና፣ የሰብዓዊ እና ማህበራዊ ልማት ኮሚሽነር ሆነው ተመርጠዋል።

ጋናዊው አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደህንነት ኮሚሽነር ሆነው በድጋሚ መመረጣቸው ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት ሞሰስ ቪላካቲ ከአምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ፣ ሌራቶ ማታቦጅ ከአማኒ አቡ-ዘይድ (ዶ/ር) እና አምባሳደር አማ ቱም-አሞሃ ከአምባሳር ሚናታ ሳማቴ ሴሱማ ጋር አዲሱ ቦታቸውን ተረክበዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አዲስ ተመራጭ ከፍተኛ አመራሮች ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።

ተመራጮቹ በተመደቡበት ቦታ ለቀጣይ አራት ዓመታት ኮሚሽኑን ያገለግላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም