ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ከ9 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባለፉት ስድስት ወራት ከታክስ በፊት 9 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ኃይለ ሚካኤልን ጨምሮ የተቋሙ ሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ምልከታ እያደረጉ ነው።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የቢዝነስና ዴቨሎፕመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኔ ገብረእግዚአብሔር የተቋሙን የስድስት ወራት አፈፃፀም አቅርበዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ በማሳለጥ በኩል የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።

ከዕለት ፍጆታ ዕቃዎችና ሸቀጦች ጀምሮ ልዩ ልዩ የፋብሪካ ውጤቶችን፣ አነስተኛና ትላልቅ ማሽነሪዎችን፣ ተሽከርካሪዎችን፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችንና የተለያዩ ጭነቶችን በባህርና በየብስ ትራንስፖርት በማጓጓዝ የተሟላ የሎጅስቲክስ አገልግሎት እየሰጠ እንዳለም ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ቶን የገቢና የወጪ ንግድ ጭነት አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሰዋል።

ከሚሰጣቸው አገልግሎቶችም በግማሽ ዓመቱ 44 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ከ46 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልፀዋል።

ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ99 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

በዚህም ተቋሙ ከታክስ በፊት 6 ቢሊየን ብር ለማትረፍ አቅዶ 9 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን ጠቅሰዋል።

ትርፉ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ188 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ነው ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም